06/03/2026
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተዘዋውሮ በመታዘብ ባገኛቸው ጉዳዮች ላይ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሰጠው ህጋዊ የምርጫ ታዛቢነት ፈቃድ መሰረት በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሂደት ላይ በንቃት ተሳትፏ አካሂደናል ።
በፌዴሬሽኑ 54 የምርጫ አስተባባሪዎችን እና ከ2000 በላዬ ተቀማጭ የምርጫ ታዛቢዎችን በክልሉ በተለያዩ ዞኖች፣ ሪጂዮ ፖሊ ከተሞች ፣ወረዳዎች፣ ከተሞች ባሉ ምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በማሰማራት ከምርጫው ቅድመ ዝግጅት ፣ድምጽ አሰጣጥ እስከ ድምጽ ቆጠራ ድረስ ያለውን ሂደት በቅርበት ተከታትለን ታዝበናል።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 38 መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ በሀገሩ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው ይደነግጋል ። እንዲሁም አንቀጽ 25 ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን ይደነግጋል። በዚህ መሰረት ዜጎች ያለ አድልዎ እና ያለ ጫና የዴሞክራሲ መብታቸውን በመጠቀም በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሂደት ውስጥ መሳተፋቸውን ታዝበናል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR) አንቀጽ 25 እና የአፍሪካ ቻርተር ስለ ዴሞክራሲ፣ ምርጫ እና መልካም አስተዳደር የሚያስቀምጧቸው መርሆዎች ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ግልጽ እና ታማኝ ምርጫዎች መካሄድ እንዳለባቸው ይደነግጋሉ። በታዛቢዎቻችን ምልከታ መሰረት የተካሄደው ምርጫ እነዚህን መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርሆዎች ለማሳካት ጥረት መደረጉን ታዝበናል።
በክልሉ በርካታ በምርጫው ክልሎች በምርጫ ጣቢያዎች ላይ መራጮች በሰላማዊ ሁኔታ፣ በሥርዓት እና በከፍተኛ ቁርጠኝነት ድምጻቸውን መሰጠታቸውን ታዝበናል።
በተለይም የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአረጋውያን እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የሚበረታታ እና የዴሞክራሲ ባህልን የሚያጠናክር መሆኑን ታዝበናል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በማራመድ፣ ለደጋፊዎቻቸው የሰላምና የመቻቻል መልዕክቶችን በማስተላለፍ እና የህዝብን ውሳኔ ለማክበር ፈቃደኝነት በማሳየት ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ታዝበናል።
የምርጫ አስፈጻሚዎች ህግን፣ መመሪያዎችን እና የምርጫ ስነ-ምግባርን በመከተል ኃላፊነታቸውን በተጠያቂነት መንፈስ በአግባቡ መወጣታቸውን መታዘብ ችለናል ።
በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ቁሳቁሶች በወቅቱ መድረሳቸውን፣ የምርጫ ሂደቱ በሥርዓት መጀመሩን እና በተገቢው ሂደት መከናወኑን መታዘብ ችለናል ።
የፀጥታ አካላት በተለይም የክልል እና የአካባቢ ፖሊስ አባላት ህግና ሥርዓት እንዲከበር በማድረግ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ሰላም እንዲጠበቅ በመሥራት እና ዜጎች በነፃነት ድምጻቸውን እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ታዝበናል።
በአጠቃላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሁሉም አካባቢዎች ሰላማዊ፣ ግልጽ፣ አካታች እና የዴሞክራሲ መርሆዎችን ለማሳካት በተደረገ ጥረት የተካሄደ መሆኑን ታዝበናል።
የህዝባችን የዴሞክራሲ ተሳትፎ፣ የፖለቲካ ብስለት እና የሰላም ባህል በዚህ ምርጫ ሂደት ውስጥ በግልጽ ሁኔታ መንጸባረቁን ታዝበናል።
በዚህ አጋጣሚ የምርጫው ሂደት ተጠናቆ የመጨረሻ ውጤቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ወጣቶችን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ደጋፊዎቻቸውን እና መላውን ህዝባችን በተለመደው ሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ ትዕግስት እንዲያደርጉ፣ ከማንኛውም አይነት ቅስቀሳ፣ ግጭት እና ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።
በተጨማሪም የክልላችንን መልካም እሴቶች፣ አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ መቻቻል እና በሰላም አብሮ መኖር ባህላችንን በመጠበቅ ለቀጣይ የዴሞክራሲ ግንባታ ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት እንድንወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመጨረሻም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ለምርጫው ስኬት አስተዋፅኦ ላደረጉ መራጮች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፣ ሚዲያዎች እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ከልብ እናመሰግናለን ።
እንዲሁም በልዩነት የክልላችን ወጣቶች በምርጫ አሰፈጻሚነት፣ታዛቢነት፣በግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመሰጠት ፣በመራጭነትና በተመራጭነት በመሳተፍ ላደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎ ከልብ እናመሰግናለን።
"ሰላማዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ድል ሲሆን፣ የዴሞክራሲ ድል ደግሞ የህዝብ ድል ነው።"
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን
ግንቦታ 26 2018 ዓ.