06/08/2026
ፌዴራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አዲስ ተሿሚ አመራሮች የሥራ ርክክብ አደረጉ
©©©©©©©
ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም (የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የፌዴራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አዲስ የተሾሙ አመራሮች በዛሬው ዕለት የሥራ ርክክብ አድርገዋል፡፡
የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በፈቃዳቸው መልቀቂያ ባስገቡት የፌዴራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አመራሮች ምትክ በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ተመልምለው የቀረቡ እጩዎችን ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ሹመት መስጠቱ ይታወሳል።
ክቡር ሼህ መከተ ሙሄ መኮንን የፌዴራል ጠቅላይ ሼሪ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም ክቡር ሼህ አብዱልመናን መሐመድ አህመዲን የፌዴራል ጠቅላይ ሼሪዓ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሰሩ በተሾሙት መሰረት በዛሬው ዕለት ከቀድሞ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር ሼህ ሙባራክ ሼህ መሐመድ አወል እና ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር ሼህ ሸረፈዲን ሚስባህ የስራ ርክክብ አድርገዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በስራ ርክክቡ ወቅት፤ የፌዴራል ሼሪዓ ፍርድ ቤቱን እስከ ዛሬ ድረስ በፕሬዝዳንትነት እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩ አመራሮችን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው፤ በዛሬው ዕለት ኃላፊነት ለተረከቡት አዲስ አመራሮች የበለጠ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው በማሳሰብ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የስራ ርክክቡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረትን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተከናውኗል።
መረጃው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ነው።