Access to Justice Initiative - Ethiopia

Website

Access to Justice Initiative - Ethiopia Promoting the Rule of Law & Access to Justice in Ethiopia.
(2)

We empower citizens through expert legal education and awareness.
⚖️ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ዜጎች በሕግ እውቀት እንዲበቁ የሚሰራ ሙያዊ መድረክ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በስኬት ለማስጀመር ዝግጅቱን አጠናቀቀ!የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በተሻለ የ...
27/09/2026

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በስኬት ለማስጀመር ዝግጅቱን አጠናቀቀ!

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በተሻለ የመማር ማስተማር ሥርዓት ለማስጀመር ያለመ የምክክርና የግምገማ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የመምህራን፣ የተማሪዎች እና የአካዳሚክ ኮሚሽን አባላት የተሳተፉ ሲሆን፣ የ2018 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በጥልቀት ተገምግመዋል።

የውይይቱ ዋና ዋና ነጥቦችና የተሰጡ አስተያየቶች፡

የሕግ ት/ቤት ዲን ዶ/ር ካሚል አብዱ፡ ውይይቱ ያለፉትን አፈጻጸሞች በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል እና ድክመቶችን በማረም የተሻለ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

አንጋፋው መምህር አዲስ ለገሰ፡ ተማሪዎች በእውቀት፣ በክህሎት እና በስነ-ምግባር ታንጸው የፍትህ ልማት ሰራዊት እንዲሆኑ አባታዊ ምክር የለገሱ ሲሆን፣ መምህራንም ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የተማሪዎች አስተያየት፡ ተማሪዎች በ2018 ዓ.ም ያጋጠሟቸውን የጊዜ አጠቃቀም፣ የምዘና ሥርዓት እና የትምህርት ይዘቶች በወቅቱ አለመሸፈን ችግሮች አንስተው በቀጣይ ዓመት ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የጠየቁ ሲሆን፣ የአካዳሚክ ኮሚሽን አባላትም የተነሱትን ሀሳቦች እንደ ግብአት በመውሰድ ለመፍትሔው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶ/ር ቢንያም ሽመልስ፡ ሕግ ትምህርት ቤት ይህንን አርአያነት ያለው ተግባር በመስራቱ አመስግነው፣ ይህ መልካም ልምድ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች እና ኮሌጆች እንዲስፋፋ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የእውቅና አሰጣጥ፡
በመድረኩ በ2018 ዓ.ም 2ኛ ሴሚስተር የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እንዲሁም በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ መምህራን የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ወሎ ዩኒቨርስቲ — የፍቅር፣ የሰላም እና የጥበብ ዩኒቨርሲቲ

የመጀመሪያው የሹመት ዜና፦ዶ/ር አብርሃም በላይ  የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው መሾማቸው ተሰምቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀኝ እጃቸውን እዚህ ቦታ የመደቡት በም...
27/09/2026

የመጀመሪያው የሹመት ዜና፦

ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው መሾማቸው ተሰምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀኝ እጃቸውን እዚህ ቦታ የመደቡት በምክንያት ይመስለኛል።

መልካም የሥራ ዘመን

27/09/2026

አትፍረድ ይፈረድብሃል ነው ነገሩ

26/09/2026

ዝም ማለት ያለብህ ፦
1.ስኬት ሲመጣ ዝም በል 2.በማታውቀው ነገር ላይ ዝም በል 3.ሞኝ ሲከራከርህ ዝም በል 4.ሰው ሲያማህ ዝም በል 5.ሌላ ሰው ሲያወራ ዝም በል 6.በተናደድክ ጊዜ ዝም በል።

26/09/2026

ደመራው ወዴት አቅጣጫ እንደወደቀ መረጃ ወዲህማ በሉ🤲
ለሟሟረትም ለማቀሳሰርም እንዲመቸን

26/09/2026

ለልጆች መልካም አስተዳደግና ደህንነት ሲባል 'የልጆች በላጭ ጥቅም' (Best interest of the child) የሚለው የህግ መርህ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ ትልቅ ቦታ አለው።
በልጆች መብት፣ በአሳዳጊነት ወይም በተያያዥ የህግ ጉዳዮች ላይ ያላችሁን ጥያቄ እዚህ ኮሜንት ላይ አስቀምጡልን። ለጥያቄዎቻችሁ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን!

26/09/2026

ተቋማዊ ሽብር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኤቴም ማሽኖቹን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ በወሎ አካባቢ ተቋማዊ ሽብር እየፈጠረ ነው።

26/09/2026

"ታሪክ ይደገማል፤ ታሪክ ሰሪው ግን አይቀየርም!
በጉንደት በሁለት ቀን የረገፈው፣ በጉራ በሁለት ቀን ዱቄት የሆነው የጠላት ሰራዊት፤ ዛሬም የታሪኩ ማጠቃለያ ተመሳሳይ ነው!
ኢትዮጵያ ወራሪን ታፈርሳለች እንጂ አትፈርስም!
ክብር ለሀገር መከላከያ ሰራዊታችን!

26/09/2026

የህዝብን ድምፅ አለመስማት እና የደሃውን ጉሮሮ መዝጋት ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ድል አይደለም። እውነቱ ግልጽ ነው ጥጋብና ጎማ መተንፈሱ አይቀርም!

ልጆች እናታቸውን ወይም አባታቸውን የመሳሰላቸውን ጉዳይ ከመጽሐፍ መግቢያ/መቅድም ጋር በማነጻጸር  የተጻፈ ጹሁፍ አይቻለሁ። የመጽሐፉን መቅድም እና ዘርዘር ያለ መግቢያውን እንድታነቡት ጋበዝኩ...
26/09/2026

ልጆች እናታቸውን ወይም አባታቸውን የመሳሰላቸውን ጉዳይ ከመጽሐፍ መግቢያ/መቅድም ጋር በማነጻጸር የተጻፈ ጹሁፍ አይቻለሁ።

የመጽሐፉን መቅድም እና ዘርዘር ያለ መግቢያውን እንድታነቡት ጋበዝኩኝ።

መቅድም

በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ ከ60 ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት ፕ/ር አለን ሴድለር በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ የጻፉት መጽሐፍ ከአንድ ሰው አማካኝ የሕይዎት ዘመን ቆይታ (life expectancy) በላይ እስከ አሁን ድረስ በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ላይ ማብራሪያ መጽሐፍ ነው፡፡ ይኽን ያክል ዓመት ቆይተን በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ ወጥ የሆነ አታች ጹሑፍ /ማብራሪያ መጽሐፍ ለመጻፍ ድፍረት አጥተን መቆየታችን ትክክል ነው ሊባል አይችልም፡፡ አንድ የጹሁፍ ሥራ ለመጀመር በዚያው ሥራ ላይ የተሰራ ሥራ አለመኖሩን መነሻ በማድረግ ወይም ጸሐፊው ከዚህ ቀደም የተሰራው ሥራ ዘመኑን የማይዋጅ ነው ብሎ ሲረዳ የራሱን አዲስ ሥራ በማቅረብ ሊያሣካ ያሰበው ዓላማ እና ሊደፍን ያሰበው ቀዳዳ ሊኖር እንደሚችል ይታመናል፡፡ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊም ከዚህ ውጭ አይሆንም፡፡ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ እጅግ ጥልቅ፣ ውስብስብ፣ ገባኝ ሲሉት መልሶ የሚጠፋ፣ ሁልጊዜ አዲስ እና አባጣ ጎርባጣ የበዛበትን የፍትሐብሔር ፍትሕ ሥርዓት (civil justice system) የሚመራ እና የሚዘውር ሕግ ነው፡፡

አለን ሴድለር (ፕሮፌሴር) በ2006 ዓ.ም እ.ኤ.አ 2014) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በተገኙበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ቤተ መጽሐፍ ጉብኝነት ሲያደርጉ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ እሣቸው ከአዘጋጁት መጽሐፍ ውጭ ሸልፍ ላይ ሌላ የተዘጋጀ ማብራሪያ መጽሐፍ አለመኖሩን ተመልክተው “ይኽ እኮ እኔ አዲስ ተመራቂ በነበርኩበት ወቅት የጻፍኩት መጽሐፍ ነው፤ እስከዚህ ዓመት ድረስ እኔ ከጻፍኩት መጽሐፍ ውጭ ለምን ማብራሪያ መጽሐፍ አልጻፋችሁም?” በማለት ቁጭት አዘል ንግግር አድርገው እንደነበር በወቅቱ አለን ሴድለርን ሲያስጎበኙ የነበሩ አንድ ታዋቂ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ለጸሐፊው አጫውተውታል፡፡ እንደ ጸሐፊው እምነት ከአለን ሴድለር ማብራሪያ መጽሐፍ ውጭ 60 ዓመት ሙሉ ቆይተን እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ላይ ወጥ እና የተጠቃለለ ማብራሪያ መጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለተደራሲያን አለመቅረቡ ያስቆጫል፡፡

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ የመረጠው ርዕሰ ጉዳይ በኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ በጠቅላላው ሆኖ ስለ ሕጉ ክፍተት፣ አተግባበር እና መሟያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ 11 ዓመት ገደማ ሊወስድበት ችሏል፡፡ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ ክፍተቶችን መለየት፣ በተግባር የሚስተዋሉ ችግሮች ማሣየት፣ የማሻሻያ ሃሳብ ጭምር መስጠት እና ከተለመደው ንባብ ወጣ ብሎ የበርካታ ሀገራትን ፍትሐ ብሔር ሥነሥርዓት ሕግጋት ጥናት ማድረግ ለእኛ ሀገር የፍትሐብሔር ፍትሕ ሥርዓት አጋዥ የሚሆን አዳዲስ ሀሳብ ማምጣት እጅግ ከባድ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ “እንደ ጣና ሃይቅ እጅግ ጥልቅ፣ እንደ አባይ ወንዝ እጅግ ሰፊ” ሆኖ ጥናት ያልተደረገበት፣ ብዙም ያልተጻፈበት ሁልጊዜ አዲስ ሕግ ነው፡፡ የተጋነነ ቢሆንም የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ሁልጊዜ አዲስ መስሎ የመታየቱን ጉዳይ መግለጽ የሚቻለው የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ እና ሞት ተመሣሣይ ናቸው፤ ሁልጊዜ አዲስ፡፡

ጸሐፊው የከ100 ሀገራት በላይ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ላይ በቂ ንባብ አድርጓል፡፡ የሌሎች ሀገራትን ሥነሥርዓት ሕግ ስንመለከት የእኛ ሕግ ስንጥቅ ቁልጭ ብሎ ይታያል፤ መጨመር እና መካተት ያላባቸው አዳዲስ ድንጋጌዎች ይኖራሉ፡፡ ከትንሽ ጉዳይ ብንነሣ እንኳን ከዓለም አቀፉ ተሞክሮ በመውሰድ እየተጠቀምን ነው ከሚባል በስተቀር የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ በግልጽ ያስቀመጣቸው መርሄዎች የሉትም፡፡ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ውስጥ መርህ መሆን የሚችሉ ድንጋጌዎች ያሉ ለመነሻ ከሚሆኑት ውስጥ በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት፤[1] የመሰማት መብት፤[2] እና ሌሎች ይኙበታል፡፡ በርካታ ሀገራት ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸውን ሲያወጡ ሕጉን ሊሸከሙ የሚችሉ ጠቅላላ መርሆዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ ኤርትራ እ.ኤ.አ 2015 የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጓን ስታወጣ የጀመረችው በመርህ ድንጋጌዎች ነው፡፡[3] ከሕንድ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ወጣ ብሎ የሌሎች ሀገራትን ሕግ ማየት ጊዜው ይጠይቃል፡፡ ለዚያው ነው ጸሐፊው የበርካታ ሀገራት ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ለመዳስ የተገደደው፡፡[4] በእኛ ሀገር አንዳንድ መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ጹሑፎችን ስናዘጋጅ የምናጣቅሰው የሕንዱን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ነው፡፡ በጸሐፊው እምነት ይህ ትክክል አይደለም፤ የሌሎች ሀገራትን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻ ሣይሆን የሕንድ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ እ.ኤአ. በ1908 የወጣው ሲሆን እ.ኤ.አ 1909 ጀምሮ እስከ እ.ኤ.አ 1976 ድረስ 31 (ሰላሣ አንድ) ጊዜ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ ከ1977 እስከ 2022 እ.ኤ.አ 20 (ሃያ) ጊዜ በአጠቃላይ 52 ጊዜ የተሻሻለ መሆኑን መረጃዎች ያሣያሉ፡፡ እንደ ፍርድ ቤት ክርክር “ጹሑፍ” አንድ ቦታ ላይ ማቆም ስላለበት እንጂ ጸሐፊው የኢትዮጵያን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ጽፎ አልጨ ረሰውም፡፡

በኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ላይ ከሴድለር በስተቀር የተጠቃለለና ወጥ የሆነ ማብራሪያ መጽሐፍ ከአለመኖሩ የተነሣ እና ሴድለርም ቢሆን ከ60 ዓመት በፊት ተዘጋጅቶ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘመኑን ለመዋጀት መቸገሩ አይቀሬ ነው፡፡ በሕግ ትምህርት ቤት ሣይቀር ለማስተማሪያነት የምንጠቀመው ይኽንኑ መጽሐፍ ከመሆኑ የተነሣ ጸሐፊው አሁን የምታነቡትን ግዙፍ መጽሐፍ ለመጻፍ ወስኖ ሲነሣ እና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በምታዩት ልክ ለፍጻሜ ሲደርስ ጸሐፊው ራሱን “ውዝፍ ዕዳ እንዳለበት ባለዕዳ ሰው በመቁጠር፡ ብድሩን የከፈለ ባለዕዳ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡” ጸሐፊው ይኽን ሥራ የጀመረው ህዳር 03 ቀን 2008 ዓ.ም ሲሆን ሥራው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው ሐምሌ መጨረሻ 2018 ዓ.ም ነው፡፡ ጸሐፊው በእነዚህ አሥራ አንድ ዓመታት ውስጥ ዋና ሥራ አድርጎ ሲሰራ የነበረው ይኽንኑ መጸሐፍ መሥራት እና ማዋለድ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶት ይኽው ተወልዷል፡፡

መግቢያ

1. The Encyclopedic Commentary….

በመጽሐፉ አርዕስት “Encyclopedic” የሚል መሪ ቃል ተመልክቷል፡፡ “Encyclopedic” አቻ የአማርኛ ትርጉም “ዓውደ ጥበብ” ማለት ነው፤ የጥበብ ዓውድ፡፡ በዚህ ለመጽሐፉ አርዕስትነት “Encyclopedic” ሲባል የብዙ ነገር ድምር ወይም ጥቅል ማለት ስለሆነ “የተጠቃለለ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ይህ መጽሐፍ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን በጠቅላላው አተግባበሩን፣ ክፍተቱን እና ማሟያውን እንዲ መለከት ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑ፤ የበርካታ ሀገራትን ልምድ ያካተተ፤ የእኛ ሀገር ፍርድ ቤቶች በየዕለቱ በሚባል ደረጃ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ ያላቸውን አተያይ ስለሚያሣይ እና በዚያው ልክ በይዘቱም ገዘፍ ያለ መጽሐፍ ስለሆነም “Encyclopedic Commentary on the Civil Procedure Code of Ethiopia” በሚል ሊሰዬም ችሏል፡፡ መጽሐፉ ወደፊት ጊዜ እና ሁኔታ ሲፈቅድ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ የመምጣት ዕድል ስለሚኖረው ስያሜው ከወዲሁ ፈር እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ መጽሐፉ በ52 ምዕራፎች ተከፋፍሎ ቀርቧል፡፡

ይኽን መጽሐፍ የተጠቃለለ (Encyclopedic) ብሎ ለመጥራት ቢያንስ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡- (1) መጽሐፉ የኢትዮጵያን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ክፍተቱን እየለየ፣ አተገባበሩን እየፈተሸ፣ የማሻሻያ ሃሳቦችን በማሣየት ወጥ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ ማብራርያ መሆኑ፤ (2) ሰበር ሰሚ ችሎቱ ብቻ ሣይሆን ከመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር አጣሪ ችሎት ድረስ ያለውን የፍትሐ ብሔር ፍትሕ ሥርዓት የሙግት አመራር የሚመረምር እና የመፍትሄ ሃሳብ የሚያስቀምጥ መሆኑ፤ (3) ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት የከ100 ሀገራት በላይ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግጋት ጥቅም ላይ የዋሉ መሆናቸው እና በርከት ያሉ ሕጎችን ስንመለከት የእኛን ሀገር ሕግ ስንጥቅ አጉልቶ ስለሚያሣይ የማሻሻያ ሃሳብ ለመስጠት እና በአጠቃላይ ለፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አስተምህሮት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩ ናቸው፡፡

የመጽሐፉ ሁሉም ምዕራፎች እና ንዑስ ርዕሰ ጉዳዮች ስለ አተግባበር፣ ክፍተት እና ሟሟያን በተመለከተ ከሀገራችን ፍርድ ቤቶች የዕለት ተዕለት ገቢራዊ እንቅስቃሴ (practical approach)፣ ትምህርታዊ ዓላማን (academic approach)፣ መረጃ ሰጭነትን (informative approach) እና ለእኛ የሚጠቅሙ የበርካታ ሀገራትን ልምድ ባንድ ላይ አዋዶና አዛምዶ የሚዳስስ መጽሐፍ መሆኑን ጸሐፊው በብርቱ ያምናል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ መጽሐፉን “Encyclopedic Commentary on the Civil Procedure Code of Ethiopia” የሚል ስያሜ ይዞ ፊት ለፊት “practice, gaps and gap filling in a Global Context” የሚል ረጅም ሐረግ ተጨምሮበታል፡፡ የመጽሐፍ አርዕስት የመጽሐፉ ተሸካሚ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፤ይኽም ሆኖ ዋናው የውስጥ ይዘት ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ከአንባቢያን አንዳንድ አስተያየቶችን በመቀበል እና የተመረጡ አለም ዓቀፍ የፍትሐብሔር ውሣኔዎችን አካቶ ከዚህ በላይ በሃሳብም በመጠንም ገዘፍ ብሎ ተሻሽሎ ይመጣል፡፡

1. ይህ መጽሐፍ ከሴድለር የተለዬ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

ከመጽሐፉ ዝነኝነት እና ዕድሜ፣ አንድ ለእናቱ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ስያሜውን ከጸሐፊው ስም የወሰደው ሴድለር በ1958 ዓ.ም የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ በወጣ ማግስት፣ ሕጉ በተግባር ሣይፈተን የመጀመርያው ማብራሪያ መጽሐፍ የተጻፈው በፕሮፌሴር አለን ሴድለር ነው፡፡ ተደራሲያኑ በተለይ የሕግ ማህበረሰቡ ሊያውቀው የሚፈልገው ጉዳይ ቢኖር ይህ “የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ፣ አተገባበር፣ ክፍተት እና ማሟያ” የሚል ስም የተሰጠው ማብራሪያ መጽሐፍ ከሴድለር የተለዬ ነገር ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ? የሚለውን ነው፡፡ በእርግጥም መነሣትና መመለስም ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ከ1958 ዓ.ም ወዲህ ማለትም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ከሕገ መንግሥት ጀምሮ እስከ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ዓለማቀፍ ስምምነቶች፣ እጅግ በርከት ያሉ አዋጆች፣ የሰበር ውሣኔዎች፣ የሕግ እና የማኅበረሰብ ተለዋዋጭ ባህሪ (legal and social dynamism)፣ የተከራካሪ ወገኖች ብዛት፣ የጉዳዮች ዓይነት፣ ብዛት እና ውስብስብነት “ሴድለር” ዘመኑን ለመዋጀት መቸገሩ አልቀረም፡፡ ዘመናዊውን የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ (Contomporary Civil Procedure Laws) ዞር ብሎ ማየት የግድ ይላል፡፡ ጸሐፊው የከ100 ሀገራት በላይ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግጋትን ለመዳሰስ ምክንያት የሆነውም ይኽው ነው፡፡

በዓለም ላይ ያለውን ዘመናዊነት በመከተል ሥነሥርዓታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ (Procedural Paradigm Shift) እየተደረገ መሆኑን የምንረዳው እኛ ሕጉን ከሕንድ ሀገር ከቀዳንበት 1958 ዓ.ም በኋላም ሆነ በፊት የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸውን ያወጡትን ወይም ያሻሻሉትን ሀገራት ስንመለከት ነው፡፡ ወደ ሌላ ሀገር ከመሄዳችን በፊት ከእኛ ጋር የሥርዓተ ሕግ ተካፍሎት የነበራት ኤርትራ በ2015 እ.ኤ.አ ያሻሻለችውን የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አዳዲስ ሃሳቦችን ጨምሮ የመጣ መሆኑን ይመለከቷል፡፡[5] የትናንት ሀገር አዲሲቷ ሱዳን ጭምር አዳዲስ ሃሳቦችን የያዘ የሥነሥርዓት ሕግ አውጥታለች፡፡[6]

በጸሐፊው እምነት የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ብዙም ጥናት ያልተደረገበት የሕግ ክፍል፣ አልፎ አልፎ ተግባር ያልተመለከታቸው እና የተረሱ የሚመስሉ ድንጋጌዎች ጭምር ያሉበት ሕግ ነው፡፡ በቁጥር ቀላል የማይባሉ ድንጋጌዎች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ አይግባቡም፤ የእንግሊዝኛው ድንጋጌ ወደ አማርኛ ያልተተረጎሙበት አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ አንዳንድ ድንጋጌዎች ደግሞ ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ ያልተተረጎሙበት አገጣሚም እንዲሁ፡፡ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ከፍተቶች በተለያዬ መንገድ ወደፊት እንዲመጡ ሲደረግም አይስተዋልም፡፡ አለን ሴድለር በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ አታች ጹሁፍ የጻፉበት ወቅት ሕጉ በወጣ ማግስት፡ በተግባር ሣይፈተን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሕጉን እና አተገባባሩን (the law and practice) እየተከታተሉ ከፍተቶችን ለመለየት ዕድል አላገኙም ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሣይሆን የአለን ሴድለር አታች ጹሁፍ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን አንቀጽ በአንቀጽ ለማብራራት ያለመ አለመሆኑን ራሣቸው በመጽሐፋቸው መንደርደሪያ አሳውቀዋል፣[7] በድጋሜ ይኽንኑ ቃላቸውን አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡[8] ሴድለር ማብራሪያ መጽሐፉን ሲጽፉ የተጠቀሙት የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን የእንግሊዝኛውን ክፍል ብቻ ስለሆነ በሥነሥርዓት ሕጉ ውስጥ ከእንግሊዝኛው ወደ አማርኛ ያልተተረጎሙ ድንጋጌዎችን፣ ሐረጋትን እና አናቅጽን ለመለየት አያስችላቸውም፡፡ ይህ በራሱ ቀላል የማይባል ክፍተት ይፈጥራል፤ በተግባርም የምናያቸው ጉዳዮች አሉ፡፡

ይህ አሁን የምታነቡት መጽሐፍ የበርካታ ሀገራትን የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ለእኛ ሀገር በሚጠቅም እና ክፍተት ሊሞላ በሚያስችል መልኩ በማነጻጸር፣ እና ያልተደጋገሙ የሰበር ውሣኔዎችንም በመመልከት የቀረበ በመሆኑ፤ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን ድንጋጌዎች አማርኛውን ከእንግሊዝኛው ጋር እያመሳከረ እና ችግሮቹን እየለዬ መሰናዳቱ፤ ጸሐፊው በጥብቅና በያዛቸው ጉዳዮችም ሆነ ለጹሑፉ ዓላማ ግብአት ለመሰብሰብ በበርካታ ችሎቶች በመታደም የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን አተግባበርና ክፍተት ተመልክቶ ለክፍተቶችም የማሻሻያ ሃሳብ ያቀረበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ “የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ፣ አተገባበር፣ ክፍተት እና ማሟያ” ከሴድለር በብዙ ነገር የተለዬ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህ መጽሐፍ የኢትዮጵያን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አተገባበሩን ያያል፤ ክፍተቶችን ይለያል፤ ለክፍተቶቹም ከተግባራዊ አሠራሮች በመነሣት፣ የሀገራትን ልምድ እና ሌሎች አማራጮችን በማየት ለመሙላት ጥረት ያደርጋል፡፡

የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ከወጣበት ዘመን ወዲህ በርካታ የሕግ ለውጦች መደረጉ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ የሰበር ውሣኔዎች መምጣት፣ ቆየት ከአለው የፍርድ ቤት ክርክር በተለዬ መልኩ አሁን ያለው የፍርድ ቤት ክርክር በዓይነትም ሆነ በብዛት መበራከተ እና በተቃራኒው ደግሞ ፕ/ር አለን ሴዴለር አታች ጹሁፉቸውን በጻፉበት ወቅት ለማፍታቻነት የተጠቀሙት የሌላ ሀገር ፍርድ ቤት ውሣኔዎችን መሆኑን በመጽሐፋቸው ላይ ገልጠዋል፡፡[9] በወቅቱ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የወሰኗቸው ውሣኔዎች እጅግ በጣም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሣ ጥናት ለማድረግ በቂ አልነበሩም፤[10] በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሰበር ሰሚ ችሎቱን ሣይጨምር በተለያዬ እርከን ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች በየዕለቱ እያከራከሩ የሚወስኗቸውን ውሣኔዎች ብዛት ለመገመት ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ውሣኔዎች የመከታተል ዕድል ከመኖሩ የተነሣ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ ያለውን አተገባበር እና ክፍተት ለማጥናት መሠረት ናቸው፡፡

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች/ችሎቶች ለጥብቅና አገልግሎት በተገኘበት ጊዜ ብቻ ሣይሆን ለትዝብት ጭምር በርካታ የፍትሐብሔር ክርክሮችን በመታደም በተግባር የሚስተዋለውን የፍትሐብሔር ክርክር አመራር እና ክፍተት በመታዘብ ለዚህ ጹሑፍ ማብራሪያነት ተጠቅሟል፡፡ ዮሐንስ ገ/ጻድቅ የተባሉ ጸሐፊ ከሊል ጊብራንን ዋቢ በማድረግ “በስንፍና ሳቢያ ተከማችቶ በገፍ ከተቀመጠ እውቀት በሥራ የተተረጐመ ትንሽ እውቀት ይበልጣል፤” የሚለውን አባባል መሠረት በማድረግ አቅም በፈቀደ መጽሐፉ ከዕለት ተዕለት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እና ኩነታት (practical movement) ባለፈ ለትምህርታዊ ዓላማም (academic purpose) እንዲጠቅም ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑ ይታመናል፡፡

መጽሐፉ የበርካታ ሀገራትን ሕግጋት፣ የእኛንም ሕግ አተገባባር፣ ክፍተት እና ማሟያ ላይ ትኩረት ያደረገ ስለሆነ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን ለማሻሻል የሚኖረው ሚና እጅግ የላቀ እንደሚሆን ጸሐፊው ያምናል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከህትመት በኋላ በሚመጡ ሞያዊ እና ምሁራዊ አስተያየቶች ተካተውበት እንደገና ተሻሽሎ፣ የተመረጡ የውጭ ሀገር የፍርድ ቤት ውሣኔዎችን ጨምሮ፣ በሃሳብ የበለጠ ገዝፎ እና ዳብሮ መምጣቱ አይቀርም፡፡ መጽሐፉ የተዘጋጀው በፍርድ ቤት ለሚከራከሩ ባለሞያዎች ብቻ ሣይሆን በሕግ ትምህርት ቤት ለሚማሩ እና ለሚያስተምሩ መሆኑንም ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ዳኞች፣ ዓቃብያነ ሕጎች፣ ነገረ ፈጆች እና ጠበቆቸ የሕግ ባለሞያዎች ተብለው እንደ አንድ አካል የምንቆጥራቸው፣ የሕግ መጽሐፍ ለማንበብ ፍላጎት ያለው ሕግ ያልተማረው ማህበረሰብ፣ የሕግ ተማሪዎች እና አስተማሪዎች በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ላይ ያላቸው ፍላጎት የተለያዬ ነው፡፡ በታቸለ መጠን የሁሉንም ፍላጎት ለማካተት ሲባል መጽሐፉን በይዘትም ሆነ በሃሳብ ግዙፍ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም መጽሐፉ ከእንከን ነጻ (blameless) ነው ሊባል አይቻልም፡፡

2. የበርካታ ሀገራት ሥነሥርዓት ሕግጋት ለምን?

በዚህ መጽሐፍ ዝግጅት ጸሐፊው የበርካታ ሀገራትን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ መጠቀሙን መነሻ በማድረግ የተወሰኑ ሀገራትን ሕግ በልምድነት ማምጣት አይሻልሞ ወይ? የዚህን ሁሉ ሀገር ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ (100 +) በልምድነት ማምጣት ለምን ያስፈልጋል? የሚሉ ባለሞያዎች ከህትመት በፊት ጥያቄ ያቀረቡ ስለሆነ ምን አልባት ጥያቄውን ሌሎች ባለሞያዎች የሚጋሩት ከሆነ እንደ ጸሐፊው እምነት እና ምልከታ የበርካታ ሀገራን ሕግ ለመጠቀም ገፊ ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን ውስን ነጥቦች ለማቅረብ ተገዷል፡፡ ተደራሲያን (በተለይ የሕግ ባለሞያዎች) ማዎቅ ያለባቸው ጸሐፊው በማጣቀሻነት የዘረዘራቸውን ሀገራት ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ የውስጥ ይዘታቸውን በሚገባ በመመልከት እንጂ በጨረፍታ ንባብ አይደለም፡፡

ይህ መጽሐፍ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን ሙሉ ድንጋጌዎች እያሰፋ ለማብራራት፣ ተግባሩን እና ክፍተቱን በመለየት ማሟያዎችን ጭምር የሚተነትን ነው፡፡ ክፍተት እና ማሟያ ፍርድ ቤቶች ሰበር ችሎትን ጨምሮ ከሚወስኗቸው ውሣኔዎች ብቻ ሣይሆን ከሌሎች ሀገራት ሕግ ልምድ በመውሰድ ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ እንደ ማጣቀሻነት ጥቅም ላይ የዋሉት የከ100 ሀገራት በላይ ፍትሐ ብሔር ሥነሥርዓት ሕግጋት ከእኛ ሕግ ጋር ስናነጻጽራቸው አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም፤ የተለያዩ ይዘት እና ሀሳብ አላቸው፡፡ ከአንዱ ሀገር ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ያለው ዘመናዊ ሃሳብ ከሌላው ሀገር ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ የማይገኝበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡

የመጽሐፉ እያንዳንዱ ንዑስ ርዕሰ ጉዳይ የሀገራትን ልምድ አካቶ ይዟል፡፡ ለመነሻ ያክል፡- ስለ ጣልቃ ገብ ተከራካሪ ወገን የጀርመን፣ የፈረንሣይ፣ የኤርትራ፣ የፊሊፒንስ፣ የታይዋን እና የፖርቱጋል ሥነሥርዓት ሕግ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በዋናነት ስለ ጣልቃ ገብ የተወሰዱ ልምዶች፡- ይግባኝ ላይ ጣልቃ ገብቶ ስለመከራከር፣ ባል ተከራካሪ በሆነበት ሙግት የሚስት ጣልቃ ገብነት እንደ ሁኔው ክልክል ስለመሆኑ (spouse intervention-forbiden)፣ ጣልቃ ገቡ ከማን ጋር መከራከር እንደሚችል (ከሳሽን ወይስ ተከሳሽን፣ ነው ወይስ ሁለቱንም)፣ ጣልቃ ገብ የራሱን መብት ለማስከበር የሚከራከርበት ሙግት (main intervention)፣ ጣልቃ ገብ ከከሳሽ ጋር ሆኖ ተከሳሽን የሚከራከርበት ወይም ከተከሳሽ ጋር ሆኖ ከሳሽን የሚከራከርበት ጣልቃ ገብነት (supportive intervention)፣ የጣልቃ ገብ አቤቱታ መቅረብ ያለበት ክስ ለመስማት በተያዘበት ቀነ ቀጠሮ ስለመሆኑ (at first hearing)፣ የመሣሰሉት ልምዶች የተካተቱ ሲሆን በአንድም በሌላ መንገድ የእኛን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ የሚመለከቱ እና ክፍተትም የሚሞሉ ናቸው፡፡

ከዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ ጋር በተያያዘ የስፔን፣ የሩዋንዳ፣ የሞንጎሊያ፣ የአርመንያ፣ የአዲሲቷ ሱዳን፣ የኢራቅ፣ የኤርትራ፣ የጂቡቲ እና የቻይና ሀገራት ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ እንደ ሀገር ስለ ዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ (review of judgment) ከእነዚህ ሀገራት የምንወስዳቸውን ጥሩ ልምዶች እንመልከት፡- ዳግም ዳኝነት ይታይልኝ ሲፈቀድም ሆነ ሲከለከል አንድ ጊዜ ይግባኝ ሊፈቀድ እንደሚገባው፤ የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ቀደም ብሎ ፍርዱን ለፈረደው ዳኛ መቅረብ የሌለበት ስለመሆኑ፣ የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ አቅራቢው ዋስትና ገንዘብ ማስያዝ ያለበት ስለመሆኑ፣ የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ ከሁለት ጊዜ በላይ ሊቀርብ እንደማይገባ፣ የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ በይርጋ ሊታገድ የሚገባው ስለመሆኑ፣ ከፊል የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው አካላት የሰጡት አስተዳደራዊ ውሣኔ ላይ የሚቀርብ የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ ጥያቄ እንዴት መቅረብ እንዳለበት፣ ማስተባበያ ማስረጃ ስንት ጊዜ ሊቀርብ እንደሚችል እና የመሣሰሉትን አዳዲስ ሃሳቦችን እናገኛለን፡፡

በአጠቃላይ ውድ አንባቢያን ከላይ ከተገለጠው በተጨማሪ ከዚህ በታች የተወሰኑትን የሀገራት ልምድ በመመልከት ጸሐፊው ለዚህ መጽሐፍ ዝግጅት የበርካታ ሀገራትን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ መጠቀሙ ትክክል ነው ወይስ ትክክል አይደለም? የሚለውን ጥያቄ ይመልሣል ብሎ ያምናል፡፡ በተግባር ከሚያጋጥሟቹህ ጉዳዮች ተነስታቹህ የዚህ ዓይነት ድንጋጌ በእኛ ሀገር ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቢኖር ምን አለበት? የሚል ጥያቄ ለራሣቹህ አንስታቹህ ይሆናል፡፡ ወይም ወደፊት ያጋጥማቹሃል፡፡

ከክስ በፊት የእግድ ትእዛዝ አስፈላጊነት እና እግዱ የሚቆይበትን ጊዜ ወስነው የሚያልፉ ሀገራት አሉ፤[11] ይኽን ጉዳይ እኛ የተለማመድነው በቅርቡ ነው፡፡[12] በእኛ ሀገር እጅግ በተጋነነ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ምክንያት አንድን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ፈተና እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ረገድ የዳኝነት ክፍያ በቅድመ ክፍያ (advance payment) ሊሆን እንደሚገባ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸው ድንጋጌ ቀርጸው ሥራ ላይ ያዋሉ ሀገራት አሉ፡፡[13] ተከራካሪ ወገኖች ክሳቸውን አሰምተው የሚጨርሱበትን የጊዜ ሰሌዳ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸው በደቂቃ ወስነው የሚያልፉ ሀገራት አሉ (ለከሳሽ 20 ደቂቃ፣ ለተከሳሽ 20 ደቂቃ) በሚል፡፡[14] በእኛ ሀገር ክስ መስማት ጭቅጭቅ እንጂ ክርክር እስከማይመስል ድረስ እንኳንስ በደቂቃ በሰዓታት አይጠናቀቅም፡፡ የክርክር ሥርዓታችን በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት ስለማይመራ እጅግ ግብስብስ፤ ፍሬውን ከገለባ መለየት የተሣነው ነው፡፡

ከጨረታ ጋር ተያይዞ በተለይ ደግሞ በመጀመሪያው ጨረታ ለቀረበው ከፍተኛ ዋጋ አሸናፊ የሆነው ተጫራች ባቀረበው ዋጋ መሠረት በተቀመጠው ጊዜ መሠረት የሽያጭ ዋጋውን ባለመክፈሉ የተነሣ ንብረቱ ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ በሚወጣበት ወቅት በዝቅተኛ ዋጋ የመሸጥ ዕድል ይኖረዋል፤ በተግባርም ይስተዋላል፡፡ በዚህ የሚጎዳው የፍርድ ባለዕዳው ሲሆን በመጀመሪያው የጨረታ ዋጋ እና በሁለተኛው የጨረታ ዋጋ መካከል ያለውን ልዩነት የመሸፈን ግዴታ ያለበት የመጀመሪያውን ጨረታ አሸንፎ ገንዘቡን ባለመክፈሉ ምክንያት የተነሣ ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ እንዲወጣ አድርጎ ንብረቱ በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጥ ያደረገው ሰው ነው፡፡ ይኽም ቢሆን ተጎጂው አካል ክስ አቅርቦ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነው፡፡

አንዳንድ ሀገራት የመጀመሪያው ተጫራች በጨረታው አሸናፊነቱ መሠረት ገንዘቡን ባመክፈሉ የተነሣ ያው ንብረት ለሁለተኛ ጊዜ በጨረታ ወጥቶ በዝቅተኛ ዋጋ በሚሸጥበት ወቅት የመጀመሪያው የጨረታ አሸናፊ የሁለቱን ጨረታዎች የዋጋ ልዩነት እና ሌሎች ወጭዎችን የመክፈል ግዴታ ብቻ ሣይሆን እስከ አንድ ዓመት እሥራት የሚያስቀጣ ስለሆነ የእሥራት ቅጣቱ ባረፈበት በ15 ቀናት ውስጥ መክፈል ያለበት ገንዘብ ከከፈለ በኋላ ከእሥር ሊፈታ የሚያስችል ሕግ አውጥተው ሥራ ላይ አውለዋል፡፡[15] ይኽ ብቻ ሣይሆን በሌሎች ጨረታዎች እንዳይሳተፍ ገደብ ይጣልበታል፡፡ የዚህ ዓይነቱን ሂደት መከተል ጤናማ፣ ወጭ ቆጣቢ እና እምነት የሚጣልበት የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ብቻ ሣይሆን የፍርድ ቤትን እና/ወይም ፍርድ የሚያስፈጽሙትን አካላት ሥራ ቀላል ያደርጋል፡፡ ከምንም በላይ ግን በድጋሜ ጨረታ ምክንያት ንብረቱ በዝቅተኛ ዋጋ በመሸጡ ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸው የፍርድ ባለዕዳዎች /ባለንብረቶች ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ ሣያስፈልጋቸው በአቋራጭ እንዲካሱ ማድረግ ዘመናዊ የፍትሕ አሰጣጥ ሂደት ነው፡፡

ሥልጣን የሌለው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ እንደ ፍርድ የማይቆጠር ወይም ዋጋ የሌለው መሆኑን በርካታ ሀገራት በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸው ግልጽ ድንጋጌ ቀርጸዋል፡፡[16] ተከሳሽ የፍርድ ቤት መጥሪያ በአግባቡ ደርሶት ካልቀረበ የቀረበበትን ክስ እንዳመነ ተቆጥሮ (presumption of admission of the content of the plaint) ውሣኔ የሚሰጥ መሆኑን በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸው ግልጽ ድንጋጌ በመቅረጽ ሥራ ላይ ያዋሉ ሀገራት አሉ፤[17] በከሳሽ እና በተከሳሽ ስምምነት ክስ ተዛውሮ (change of venue by agreement) እንዲታይ የሚፈቅዱ ሀገራትም አሉ፡፡[18] በእኛ ሀገር ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ የክስ ይሻሻልልኝ ጥያቄ ከአንድ ጊዜ በላይ ማቅረብ ይችላሉ ወይስ አይችሉም? የሚለውም ጥያቄ ሕጉ አይመልስም፡፡ አንዳንድ ሀገራት ክሱ በውሣኔ ከመዘጋቱ በፊት ከሁለት ጊዜ በላይ የክስ ይሻሻልልኝ ጥያቄ ማቅረብ እንደማይቻል በሥነሥርዓት ሕጋቸው ገደብ ያስቀምጣሉ፡፡[19]

አንድ ምስክር ብቻ በመስማት ውሣኔ መስጠት የሚቻል መሆኑን ግልጽ ድንጋጌ ቀርጸው ሥራ ላይ ያዋሉ ሀገራት አሉ፤[20] በእኛ ሀገር ፍርድ ቤት አንድ ምስክር መስማት የተከለከለ እስከሚመስል ድረስ ነው የሚስተዋለው፡፡ ተከራካሪ ወገኖች እንደ ተመቻቸው ሣይሆን በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸው የምስክሮችን ብዛት ወስነው የሚያልፉ ሀገራት አሉ፡፡[21] በእኛ ሀገር የዚህ ዓይነት ገደብ ካለመኖሩ የተነሣ በርካታ ምስክሮችን ዘርዝሮ ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ተከራካሪ ወገኖች በቃኝ ካላሉ በቀር ፍርድ ቤቶች የቀረቡትን ምስክሮች ሁሉ ይሰማሉ፣ ካልሰማ በተከራካሪ ወገኖች በኩል ምስክሮቼን እንዳላሰማ ክልከላ ተደርጎብኘል (የመደመጥ መብት) እያሉ የይግባኝ ቅሬታ ምክንያት ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡ በእኛ ሀገር ምስክሮች ማስታወሻ እየተመለከቱ የምስክርነት ቃላቸውን ከመስጠት ሕጉ ባይከለክልም ተግባሩ ሲከለክላቸው ይስተዋላል፡፡ ማስታወሻ እየተመለከቱ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ የሚፈቅድ ሕግ የሚቀርጹ ሀገራት አሉ፤[22] የሚከለክሉም አሉ፡፡[23] በእኛ ሀገር ሕጉ በግልጽ ባይከለክልም ተግባሩ ሲከለክለው ይስተዋላል፡፡ በእኛ ሀገር ከዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ ጋር ተያይዞ ከፊል የአንድ ወር ይርጋ (partial period of limitation) ከመቀመጡ በቀር ይርጋ አልባ ነው፡፡ ውሣኔው የተሰጠ መሆኑን በአወቀ በ60 ቀናት ውስጥ የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ ጥያቄ ማቅረብ የሚቻል ሲሆን ውሣኔ ከተሰጠ 10 ዓመት ከአለፈው በማናቸውም ምክንያት ቢሆን የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ማቅረብ እንደማይቻል ድንጋጌ የሚቀርጹ ሀገራት አሉ፡፡[24] የአምስት ዓመት ይርጋም የሚያስቀምጡ ሀገራት አሉ፡፡[25] በእኛ ሀገር የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ ጥያቄ ስንት ጊዜ ማቅረብ/መጠየቅ (ሁለት ጊዜ፣ ሦስት ጊዜ፣ አራት ጊዜ) እንደሚቻል ሕጉ የሚለው ነገር የለም፡፡ የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ከአንድ ጊዜ በላይ ማቅረብ እንደማይቻል ድንጋጌ የሚቀርጹ ሀገራት አሉ፡፡[26] በእኛ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 358 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሠረት የመቃወም አቤቱታ የሚቀርበው የተሰጠው ፍርድ ከመፈጸሙ በፊት ከሚል በቀር ይርጋ አልባ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የተሰጠውን ውሣኔ በአወቀ በ60 ቀን ውስጥ ሆኖ ፍርዱ ከመፈጸሙ በፊት ሊቀርብ እንደሚገባ ድንጋጌ የሚቀርጹ ሀገራት አሉ፡፡[27] የተከሳሽ ከሳሽ አቤቱታ (counter claim/counter charges/cross action /collateral attack) ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት እንዲቀርብ የሚፈቅድ ድንጋጌ የሚቀርጹ ሀገራት አሉ፤[28] ይኽ ነገር በእኛ ሀገር የሥነሥርዓት ሕጉ ከመከላከያ መልስ ጋር መቅረብ ያለበት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ አልፎ አልፎ ፍርድ ቤቶች ከሥነሥርዓት ሕጉ ውጭ ሲያስተናግዱ ይስተዋላል፡፡ ለመነሻ ያክል በዚህ ካልበቃን ከመስመር ያስወጣናል፡፡

ከፍ ተብሎ እንደተገለጠው ለዚህ መጽሐፍ ዝግጅት የበርካታ ሀገራት ሕግጋት ጥቅም ላይ የዋሉ ስለሆነ ስለ የንጽጽር ጥናት (comparative study) አንዳንድ ነጥቦችን ማንሣት ያስፈልጋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ተነጻጻሪ ጥናት ጠቀሜታው የጎላ ነው፤ ጥናት ስለሚደረገው ሕግ ሰፊ ዕውቀት እና ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ አንድ ጉዳይ ሲያጋጥም ይኽንኑ ችግር ለመፍታት እና ለማፍታታት የሌላው ሀገር ሕግ ምን ይላል? ብሎ ማየት ተመካሪም አስተማሪም ነው፡፡[29] ተነጻጻሪ ጥናት ሕግ ለማሻሻል፣ የንባብ ልምድን ለማዳበር፣ እና ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚኖረው ሚና በእጅጉ የላቀ ነው፤ አተያይም ያሰፋል፤ የንባብ ልምድም ያዳብራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሕግ ምሁራን ይስማማሉ[30] የሀገራችን ፍርድ ቤቶች በተለይ ደግሞ ሰበር ሰሚ ችሎት ከፍተት ባለባቸው የሥነሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ላይ ትርጉም ከመስጠት አለፍ ብሎ ከእኛ ሀገር ጋር ተመሣሣይ ወይም/እና ተቃራኒ ሥርዓተ ሕግ የሚከተሉትን ሀገራት የሥነሥርዓት ሕግ የፍርድ ሀቲት አካል ቢያደርግ የሀገሪቱን የሕግ ሣይንስ ለማሣደግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥም አልፎ አልፎ ሲጠቅስ ይስተዋላል፡፡

የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ከመውጣቱ በፊት የነበሩት ዳኞች የሌሎች ሀገራትን ሕግ በመጥቀስ ፍርድ ሲሰጡ እንደነበር ቆየት ያሉ የፍርድ ውሣኔዎች ያሣያሉ፡፡[31] አሁንም ቢሆን ሰበር ሰሚ ችሎቱ አልፎ አልፎ ለሚሰጠው ውሣኔ የተለያዩ ሀገራትን ልምድ ለማየት ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በርካታ አገሮች ለምሣሌ ሩሲያ ከሟች ወደ ወራሾቹ በውርስ ሊተላለፉ የሚችሉ ንብረቶችና መብቶች በዝርዝር ያስቀምጣሉ፤[32] ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሀገራትን ስም መጥቀስ ሣያስፈልገው በርካታ ሀገራት የሚል ሐረግ ሲጠቀምም ይስተዋላል፡፡ በበርካታ ሀገራት[33] በሕግ ዕውቅና የተሰጣቸው አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች አራት ዓይነት ሲሆኑ እነዚህም ድርድር (conciliation)፣ ስምምነት (negotation)፣ የግልግል ዳኝነት (arbitration) እና እርቅ (mediation) መሆናቸውን በዙሪያው የተጻፉ ድርሣናት ያስረዳሉ፡፡ በአጠቃላይ የበርካታ ሀገራትን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ በማጣቀሻነት መጠቀም የእኛን ሀገር ሕግ ክፍተት ለመሙላት፣ ለጥናት እና ለምርምር እንዲሁም በሕግ ትምህርት ቤት ማስተማሪያት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ጸሐፊው ያምናል፡፡ በሕግ ትምህርት ቤት ስንማር እንደ ተጨማሪ ማጣቀሻነት የምንጠቀመው የሕንዱን ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ብቻ ነው፤ የእኛም የተቀዳው ከዚሁ ስለሆነ፡፡ ከዚህ በላይ ወጣ ማለት ያስፈልጋል፡፡

4. ዳኛ ሰር የሕግ ሥርዓት ከሚከተሉት ሀገራት

የእኛ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ የተወሰደው ከህንድ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሕግ ትምህርት ቤትም ሆነ አንዳንድ ጥናቶች ሲደረጉ መነሻችን ይኽው የሕንዱ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ነው፡፡ የእኛን ሀገር ሕግ ክፍተት ለመድፈን እና ሌሎች አዳዲስ ልምዶችን ለማጋራት ጠቃሚ ይሆናል የምላቸውን ጉዳዮች ለማካተት በሚል ሥርዓተ ሕጋቸውን የሕግ መድብል በማዘጋጀት (civil law countries) ከሚከተሉት ሀገራት ብቻ ሣይሆን ዳኛ ሰር የሕግ ሥርዓት የሚከተሉትን (commom law countries) ሀገራት ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጋቸውን ለመመልከት ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ በክርክር አመራር፣ በልዩ ልዩ የድንጋጌ ቅርጾች፣ የሕግ ምንጭ (source of law)፣ የፍርድ ቤቶች ውሣኔ መነሻ (ከሕግ፣ ከበልማድ ከዳበረው የፍርድ ቤቶች ውሣኔ)፣ እና ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሣኔ የአስገዳጅነት ባህሪ በሁለቱ ሥርዓተ ሕግጋት መካከል (common law and civil law legal system) ያለውን ልዩነት ማሣያ ናቸው፡፡ ሥርዓተ ሕጋቸው ንጹህ የሲብል ሕግ (pure civil law countris) የሚከተሉት ሀገራት የላቁ ፍርድ ቤቶች ውሣኔዎች ለበታች ፍርድ ቤቶች አሳማኝነት (persuasive) እንጂ አስገዳጅነት ባህሪ (binding nature) የላቸውም፡፡ ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሚሰጣቸው ውሣኔዎች ማናቸውንም የበታች ፍርድ ቤቶች ሰበር ሰሚ ችሎቱን ጭምር አስገዳጅ ናቸው፡፡

አንዳንድ የሕግ ጻህፍት “Comparing two legal disciplines is like comparing apples and oranges: both are distinctly different members of the same category.”[34] ይላሉ፡፡ ሁለቱን ሥርዓተ ሕግጋት (civil law and common law legal system) ማወዳደር ፖም እና ብርቱካን የማወዳደር ያክል ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ፈሊጣዊ አነጋገር (idoms) አንድን ነገር: “it is like apple and orange” ካልን ጭራሽ ለንጽጽር የማይቀርብ (incomparable)፤ የማይገናኙ ሁለት ጉዳዮች (two things are completely different) ማለት ነው፡፡ ከፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አኳያ ሁለቱን ሥርዓተ ሕግጋት ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው እና ለንጽጽር የማይበቁ መሆናቸውን በተመለከተው የምሁራን ጹሑፍ ጸሐፊው አይስማማም፡፡ ሌላው ቢቀር ተግባር ላይ ሲውሉ ልዩነት ቢኖርም ድንጋጌዎቹ ተመሣሣይ ናቸው፡፡ እንዳውም ዳኛ ሰር የሕግ ሥርዓት የሚከተሉት ሀገራት ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ዘመናዊ የሚባሉ ድንጋጌዎችን ሲያካትት እንመለከታለን፡፡ ከፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አኳያ በሁለቱም ሥርዓተ ሕግጋት መካከል ከልዩነት ይልቅ ተመሣሣይነት ያላቸው መሆኑን ከነባራዊ ሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ ይህ ማለት ግን ልዩነት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ዳኛ ሰር የሕግ ሥርዓት የሚከተሉ ሀገራት የተለዬ የክርክር አመራር፣ የማስረጃ አሰበሰብ እና አቀባበል አላቸው፡፡

የእኛ ሀገር ሥርዓተ ሕግ የሲቭል ሕግ ብቻ ሣይሆን በሰበር ውሣኔዎች የምንገደድ መሆኑን መነሻ በማድረግ ዳኛ ሰር የሕግ ሥርዓት (common law legal system/judge made law) ጭምር እየተከተልን ነው ወደሚለው ሊወስደን ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሣት ይቻላል፡፡ ጉዳዩን በዚህ አጭር ንዑስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ መሸፈን ባይቻልም ለመረጃ ያክል፡ (1) የዳኛ ሰር የሕግ ሥርዓት በተጻፈ ሕግ ሣይሆን ፍርድ ቤቶች በልምድ (developed court decision) ከሚወስኑት ውሣኔ በመነሣት ሌሎች የሥር ፍርድ ቤቶች እንዲከተሉት የሚያደርግ ሥርዓት ስለሆነ፤ እና የሕግ ምንጫቸው (source of law) ስለሚለያይ፤ (2) በርካታ ዳኛ ሰር ሥርዓተ ሕግ የሚከተሉት ሀገራት በመድብል ደረጃ የተደራጀ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ስላላቸው በጥቅሉ የተጻፈ ሕግ የላቸውም ማለት አለመቻሉ፤ (3) የእኛ ሀገር ሥርዓተ ሕግ ዳኛ ሰር (judge made law) ሥርዓተ ሕግ ነው ለማለት የማይቻለው ፍርድ ቤቶች ውሣኔ የሚያሣልፉት በሕግ አውጭው አካል የወጡትን ሕጎች በመተርጎም እንጂ ፍርድ ቤቶች በልማድ ካዳበሩት ውሣኔ በመነሣት አለመሆኑ እና የመሣሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አልፎ አልፎ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ክፍተትን ለመሸፈን በሚል ሕግ ማውጣት በሚመስል መልኩ የሚሰጣቸውን ውሣኔ መነሻ በማድረግ ሥርዓተ ሕጋችን በከፊል ዳኛ ሰር ነው ወደሚለው ሊወስደን ይችል ይሆናል፤ የምንከተለው ሥርዓት ሕግ ንጹህ የሆነ የሲብል ሕግ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፤ ቅልቅል እንጂ፡፡ ዳኛ ሰር የሕግ ሥርዓት በሕገ መንግሥት (የተጻፈ፣ ያልተጻፈ) እንበል እንጂ የተጻፈ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አላቸው፡፡ እንዲሁም በክርክር አመራር እና ለዳኞች የሚሰጠው ሥልጣን የተለዬ የሚያደርገው አንጻርም ይለያሉ፡፡ ከሥርዓተ ሙግትም በመነሣት በሁለቱ ሥርዓት ሕግጋት ዳኞች የሚኖራቸው ሥልጣን ይለያያል፡፡

5. በሕግ መካነ ኮሌጆች የሥነሥርዓት ሕጉ አስተምህሮት

የሕግ መካነ ኮሌጆቻችን (law schools) ስለ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ የሚከተሉት አስተምህሮት ከችግር የጸዳ ነው ሊባል አይችልም፤ ችግር ይኖርበታል፡፡ የምንከተለው ሥርዓተ ሙግት ወይም የሙግት አመራር በራሱ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉን ውጤታማ እንዲሆን በሚያስችል መንገድ መሆን አለመሆኑን የምንረዳው በተግባር ያለውን አሠራር ስንፈትሸው ነው፡፡ የሕግ ትምህርት ከተጠናቀቀ በኋላ ምሩቃን ችሎት እየቀረቡ የተግባር ልምምድ ማድረጋቸው ስለማይቀር የሚቀስሙት ልምድ መሬት ላይ ያለውን ልምድ ስለሆነ ተለማማጆች ከሕግ ውጭ ያለውን ልምድ መቅሰማቸው አይቀርም፤ ልምዱ ከችግር የተላቀቀ አይደለም፡፡ በሕግ ትምህርት ቤት የሚሰጠው የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አስተምህሮት መነሻ የምናደርገው በ1908 እ.ኤ.አ የወጣውን የሕንድ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ነው፡፡ ሕጉን ከሕንድ ስላመጣነው የአስተምህሮት መነሻችንም ይኽው የሕንዱ ሥነሥርዓት ሕግ መሆኑ ትክክል ነው፡፡ ሕንድ የመጀመርያውን የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጓን ያወጣችው እ.ኤ.አ በ1859 ነው፡፡ ይኽንን ሕግ አምስት ጊዜ አሻሽለውት የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም እ.ኤ.አ በ1908 አዲስ የሚባል የተጠቃለለ የሥነሥርዓት ሕግ አወጣች፡፡ ሕንዶች እንደ እ.ኤ.አ በ1908 ያወጡትን ሕግ ማሻሻል የጀመሩት ከአንድ ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ በ1909 መሆኑን መረጃዎች በግልጽ ይጠቁማሉ፡፡ ከ1909 እስከ 2022 ወደ 51 ጊዜ ያሻሻሉት መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም፡፡

የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ በሕግ ትምህርት ቤት የሚሰጠው በሁለት ክፍል ተከፋፍሎ ሲሆን ሕጉ በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስስ እና ከባድ ሕግም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአንድ ክፍል ሊጠናቀቅ የማይችል የትምህርት ክፍል መሆኑ ምንም ጥያቄ አያስነሣም፡፡ የጸሐፊው ልዩነት ትምህርቱ በሁለት ክፍል ከመሰጠቱ ላይ ሣይሆን አጠቃላይ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ርዕሰ ጉዳዮች ወይም ድንጋጌዎች ተቀርጸው ሲቀመጡ ባላቸው ሃሳባዊ እና ዓላማዊ ፍሰት ሣይሆን ተዘበራርቀው የተቀመጡ ናቸው የሚል ነው፡፡ ቀለል ካለ ምሣሌ ብንነሣ እንኳን አንድ የፍትሐብሔር የክስ አቤቱታ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት የከሳሹ ችሎታ፣ የክስ ምክንያት፣ የፍርድ ቤትሥልጣን እና የሚጠየቀው ዳኝነት በመግለጽ ያቀርባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ክሱ የሚያስረዱለትን የማስረጃ ዝርዝር (የሰው ወይም/እና የጹሁፍ) አያይዞ ያቀርባል፡፡ በተከሳሽ በኩል ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ፣ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ፣ አለኝ የሚለውን የመከላከያ ማስረጃ (የሰው ወይም/እና የጹሁፍ) አያይዞ ያቀርባል፡፡ የዚህ መጽሐፍ አንባቢ የመሰረተው ክስ ወይም የተመሰረተበት ክስ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ ያሉት ሥነሥርዓታዊ አካሄዶች እና የክርክር ስልቶች ሣይነጣጠሉ መቅረብ ሲገባቸው የተወሰኑትን ክፍሎች በክፍል አንድ ቀሪዎቹን ደግሞ በክፍል ሁለት ለያይተን የምናስቀምጣቸው ከሆነ አንድ ከሳሽ ወይም ተከሳሽ በክርክር ሂደት ቀደም ብሎ ማዎቅ የሚገባውን ነጥብ እንዳያውቅ ከመከልከል የሚተናነስ መስሎ አይታይም።

የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕጉ ማድመቂያ ድንጋጌዎች ከሚባሉት ውስጥ አንቀጽ 5 እና 6 መሰጠት የሚገባቸው እና ቅርበትም ያላቸው ለክፍል-1 (civil procedure code-1) እንጂ ለክፍል-2 (civil procedure code-2) መስሎ አይታይም፡፡ ዳግም ዳኝነት የይታይልኝ አቤቱታ ቀደም ብሎ የተወሰነው ፍርድ ሀሰተኛ ማስረጃን መሠረት ያደረገ መሆኑን በመግለጽ የሚቀርብ አቤቱታ ስለሆነ እና የተወሰነው ፍርድ እንዳልነበር ሆኖ አዲስ ክርክር የሚደርግበት በመሆኑ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ልክ እንደ መጀመሪያ ደረጃ ክስ ታይቶ ግንዛቤ ሊሰራበት የሚገባው በክፍል-1 የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አስተምህሮት ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 5 “ትም” ቢሆን ድንጋጌው በቀዳሚነት ስለሰፈረ ብቻ ሣይሆን ሃሳቡ በራሱ ቀደም ተብሎ ሊታወቅ እና ለከፍል-2 የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አስተምህሮት መሸጋገሪያ ይሆናል፡፡ በክፍል-1 እና በክፍል-2 መሰጠት ያለባቸውን ድንጋጌዎች በሚኖራቸው የሃሣብ ፍሰት መለየት እና የሚሸፍነውንም የጊዜ ፍጆታ ሌሎች የመስክ ልምምዶች እንደተጠበቁ ሆኖ ከ6 cr.h ወደ 7 cr.h (ክፍል-1 በ4 cr.h እና ክፍል-2 በ3 cr.h) በአጠቃላይ ወደ በ7 cr.h ከፍ ብሎ ቢሰጥ የተሻለ እንደሆነ ጸሐፊው ያምናል፡፡ ነገሩን ለሚመለከተው አካል መተውም ሌላው አማራጭ ነው፡፡

[1] የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 180
[2] እዚያው፤ ቁጥር 262
[3] The State of Eritera Civil Procedure Code, 2015. Basic Provisions. Art 1-14
[4] ጸሐፊው የከ100 ሀገራት በላይ ፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ በቂ የሚባል ዳሰሳ አድርጓል፡፡
[5] Civil Procedure Code of the State of Eritera, 2015.
[6] Laws of The New Sudan, Civil Procedure Act, 2003
[7] The book doesn’t comment on the Code, article by article, but refers to the articles of the Code and other legislation where relevant. ROBERT ALLEN SEDLER, Page vi
[8] እዚያው፤ As I stated in the preface, this book is not intended to be a commentary on the Civil Procedure Code. page 6
[9] እዚያው፤ I frequently make reference to and discuss cases that have been decided by courts of other nations. Sedler, page v
[10] እዚያው፤ ሴድለር በመጽሐፉ ጉዳዮች ማውጫ ላይ እንደተመለከተው 12 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የወሰናቸውን ውሣኔዎች ለመጽሐፋቸው ግብዓት የተጠቀሙሲሆን የእንግሊዝ ሀገር በቁጥር ወደ 50 ገደማ፤ የሕንድ ሀገር ወደ 600 ገደማ፣ የኬንያ 1፣ የናይጀሪያ 6፣ የሱዳን 8፣ የዩጋንዳ 1፣ የዌስት አፍሪካ 5 እና የአሜሪካ 46 የሚሆኑ የፍርድ ቤት ውሣኔዎችን ለማብራርያነት ተጠቀመዋል፡፡ (See Table of Cases, page Xvi-XXvI)
[11] Quebec Civil Procedure Code, 2016. Artice 510. A party may ask for an interlocutory injunction in the course of a proceeding or even before the filing of the originating application if the latter cannot be filed in a timely manner.. A provisional injunction cannot be granted for a period exceeding 10 days without the parties’ consent.
[12] እነ የማነ ግርማይ ጠ/ሥ/ ተቋራጭ ኃ/የተ/የግማ እና ቻይና ሲ ኢ ኤም ሲ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሊሚትድ፣ ቅጽ 25 የሰመ/ቁ 191402
[13] Swiss civil Procedure Code,2008. Art 98. Advance payment of costs. The court may demand that the plaintiff make an advance payment up to the amount of the expected court costs.
[14] High Court of Niger State Civil Procedure Rules 2012. Order 31, Rule 4 Oral argument. Oral argument of not more than 20 minutes shall be allowed for each party.
[15] Portuguese Code of Civil Procedue, 1939. Article 904. Payment of bid price – sanctions for non-payment. The bidder shall deposit, at the conclusion of the auction, a one tenth (1/10th) part of the price and amount corresponding to the probable expenses of the licitation without which the assets shall not be awarded to him. The balance price shall be paid within 15 days on penalty of imprisonment of the bidder and the assets going again for auction to be auctioned for any amount and the last bidder of the first auction being liable for the difference of the price and to pay costs arising from the omission. Of the second auction notice will be given by public notice and advertisement with anticipation of 7 days. The imprisonment shall not last for more than one year and shall cease as soon as the amount which was liability of the auction holder is recovered.
[16] የሕንድ፣ የስፔን፣ የአፍጋኒስቲያን፣ የናይጀሪያ፣ እና የሌሎች ሀገራት ሥነሥርዓት ሕግጋት
[17] Civil Procedure Code (Amendment of First Schedule) 2018 .Punjab Weekly Gazette August 22, 2018. In Order VIII: rule 1. Presumption of admission of contents of plaint.- When the defendant fails to present written statement of his defence before the day fixed for his hearing, the court shall presume that he admits the contents of the plaint as true: Provided that nothing shall preclude the court from permitting the defendant to present written statement, upon showing a just and sufficient cause in an application in writing supported by an affidavit.

[18] Republic of Armenia Civil Procedure Code, not official copy, 1998. Article 84. Change of jurisdiction by consent of parties.
[19] Nigrian Civil Procedure Rules 2012. Order 24 Amendment (1) Not More than twice during the trial but before close of the case.
[20] Civil Proceedings Evidence Act of Nambia, 1965. 16. Sufficiency of evidence of one witness Judgment may be given in any civil proceedings on the evidence of any single competent and credible witness.
21 Portugeuse Civil Procedure Code, 1939 Article 635 – Maximum number of witnesses which parties can examine - The plaintiff cannot offer more than 20 witnesses; equal limitation is applicable to the defendants who filed same written statement. The names of the witnesses in the list that exceed the number indicated above shall be considered not to have been written.
[22] Code of Civil Procedure of the Republic of Lithuania, 2002 Article. 193 Witness’s notes. A witness may use notes, when his evidence is related to figures or other data difficult to memorise. At the request of the judge, such notes shall be presented for the court and participants in the proceedings. The court may enclose the notes to the case.
[23] French Civil Procedure Code. Amended 2005. Article 212 Witnesses may not read from any notes.
[24] Civil Procedure Code of The State of Eritera,2015. Time of Revision. Art 400 (1) An application for revision shall be filed within sixty days when the ground for revision did arise and the applicant became aware of it, but before ten years after the judgment the revision of which is sought was rendered.
[25] Civil Procedure Code of Spain. 2015. Article 512. Time limit for lodging. 1. In no case may the review be sought after five years have elapsed from the date of publication of the judgment that it is intended to challenge. All applications for review after this time limit has elapsed shall be rejected
[26] Southern Sudan Code of Civil Procedure Act, 2007 Section 207. Review of Judgements Judgements of the Supreme Court shall be subject to review once by the same court.
[27] እዚያው ሀገር ሕግ፤ Art. 396. - Who May File Opposition. Any person who should or could have been made a party to a suit and whose interests are affected by a judgment in the suit may, if he was not a party to such suit either in person or through a representative, file an opposition to such judgment within sixty days of the day the opposing party became aware of such judgment and before such judgment is executed.
[28] Republic of Armenia Civil Procedure Code, not official copy, 1998. Article 96. Bringing a cross-action.1. The defendant, prior to the adoption of a ruling on the case, is entitled to bring a cross-action against the initial action, for joint consideration.
[29] Comparative analysis has always been part of any scholar’s toolkit. Even when analyzing purely domestic legal problems, it can be instructive to consider how other legal systems have addressed the same or similar problems. Comparative Civil Procedure and Transnational “Harmonization”: A Law and Economics Perspective, Jeffrey S. Parker, George Mason University School of Law, Revised Draft, November 2008. Page 1
[30] Comparative studies may broaden your mind and knowledge and serve as a means of illustration when teaching law at the university. (Comparative Civil Procedure by Peter GOTTWALD)
[31] ጸሐፊው ከሕግ መጽሔት ከአንደኛው ላይ የዩጋንዳን ወይም የቡሩንዲን(?) ሕግ ጠቅስው ውሣኔ ሲሰጡ ተመልክቷል፡፡
[32] ወ/ሮ ገነት እና በላይ እና ፌኔት ተክሉ፤ የሰ/መ/ቁ 44561 ቅጽ 10
[33] ደምሴ ኦዳ እና አስፋ ወርቁ፣ የሰ/መ/ቁ 196228
[34] The Oxford Handbook of Comparative Law, Mathias Reimann and Reinhard Zimmermann. Offord University Press 2006
[35] የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 244 /2/ሠ/

Address

Adis

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Access to Justice Initiative - Ethiopia posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share

Category