30/09/2026
የአስገድዶ ልመና ወንጀልን ለመቅጣት የተሟላ ህግ ቢኖርም የአፈፃፀሙ አቅም ማነስ እክል ሆኗል ተባለ
በኢትዮጵያ አስገድዶ ልመናን ለመከላከልና ወንጀለኞችን ለመቅጣት የሚያስችል ጠንካራና ዘመናዊ የህግ ማዕቀፍ ቢኖርም፤ዋነኛው ችግር የህግ ክፍተት ሳይሆን የተቋማት የአፈፃፀም አቅም ውስንነት መሆኑ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ባለሙያ አቶ ጌቱ አስነቃው ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፤የወጣው አዋጅ እጅግ ጠንካራና አስገድዶ ልመናና ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጋር በማስተሳሰር ጥብቅ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ነው ብለዋል።
ይህ የህግ ማዕቀፍ ዋና ወንጀለኞችን ብቻ ሳይሆን ወንጀሉ እንዲፈፀም ትብብር ያደረጉትን ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
ህፃናቱ ተገደዉ ለመለመን መዋላቸውን እያወቁ የመጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎችን፣ መኖሪያ ቤት የሚያከራዩ አከራዮችን እና መረጃ የሚደብቁ ግብረ-አበሮችን ጭምር በወንጀሉ ተካፋይ አድርጎ የሚያስቀጣ ሲሆን፤የቅጣት መጠኑም ከሰባት ዓመት ፅኑ እስራት ጀምሮ እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ከባድ ቅጣትን ያስቀምጣል።
ሆኖም ህጉ ይህን ያህል የጠነከረ ቢሆንም በመሬት ላይ ወርዶ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል በኩል ከፍተኛ የአፈፃፀም ማነቆዎች እንዳሉ ተጠቁሟል።
የፖሊስና የፍትህ አካላት ወንጀሉን በተገቢው መንገድ መርምረው ለፍርድ ለማቅረብ የበጀት፣ የትራንስፖርት፣የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ያለባቸው ከመሆኑም በላይ የተደራጀ ማስረጃ አሰባስቦ ጥፋተኞችን በፍርድ ቤት ለማስቀጣት የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አቅምን የሚጠይቅ መሆኑ ተብራርቷል።
ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ አካባቢ በተደረገ የሙከራ ስራ አራት የክስ መዝገቦች ተዘጋጅተው ፍርድ ቤት መድረሳቸውን የጠቆሙት የህግ ባለሙያው፤ ይህን ተግባር ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋፋት መንግስት ለህግ አስከባሪ አካላት ተገቢውን የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
መስከረም 18/2019 ዓ.ም