08/11/2025
በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም!
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰነፍና ዋልጌ ሰዎች መኖራቸው መቼም የማናስተባብለው ሐቅ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን ግን አይኮረፍም!
የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉ የምእመናን ሕይወት የማይገዳቸው፤ ስለደመወዛቸው ካልሆነ በቀር ስለምእመናን መብዛትና ስለዘለዓለም ሕይወታቸው የማያስቡ ምንደኞች ቢበዙባትም በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም!
ተናግረው የሚያናግሩ፤ ለሰው ስሜት የማይጠነቀቁ፤ አማረልኝ ብለው እንዳመጣላቸው የሚያወሩ፤ ንግግራቸው ቤተ ክርስቲያንንና አገልግሎቱን ሊጎዳ እንደሚችል ማሰብ የማይፈልጉ፤ ሥራዬ ብለው ምእመናን እንዲበተኑ የሚተጉ፤ ከሩቅ የሚመልሱ . . . ሰነፍ እረኞች ቢኖሩም በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም!
ከቤተ ክርስቲያን ወጭት እያጠቀሱ ግን ደግሞ ምእመናንን የሚያሳፍሩ፤ የሚያስቆጡ፤ የሚያስከፉና የሚገፉ . . . ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ቢኖሩም በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም!
ከዘመኑ ጋር የማይሔዱ፤ የምእመናን ሁለንተናዊ እድገትና መሻሻል ግድ የማይሰጣቸው፤ ምንም ርዕይ የሌላቸው፤ ዛሬ ብቻ እንጂ ነገ የማያሳስባቸውና የማይገዳቸው ብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ቢኖሩም በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም!
“የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” በሚል ብሒል እንጀራ የሚበሉበትን መሶብ የሚገለብጡ፤ ወርቅ ያለበሰቻቸውን ቤተ ክርስቲያን የሚያራቁቱ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ነገዋ ግድ የማይሰጣቸው ብዙ “አገልጋዮች” ቢኖሩም በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም!
በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም! . . . ምክንያቱም እርሷ እናታችን ናትና! በእናት እንዴት ይኮረፋል!!!
በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም! . . . ምክንያቱም እርሷ የነውራችን ክዳን፤ የዕርቃናችንም ልብስ ናትና!!!
በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም! . . . ምክንያቱም እርሷ ፍጽምት የምትሆን የክርስቶስ አካሉ ናትና!
በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም! . . . ምክንያቱም የአገልጋዮች ድካም የክርስቶስን ጸጋ አያስቀርብንምና፤ መስዋዕቱ እንዳያርግ፤ ምሥጢራቱም እንዳይፈጸሙ አያግዳቸውምና!!!
በቤተ ክርስቲያን አይኮረፍም! . . .
በኤዶም ኃይሉ